የመንግስት ሰራተኞች ፐርሶኔል መረጃ የማረጋገጥ ስራ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ
12 ሚያዝያ 2018
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በጋራ ለሚያካሂደው የመንግስት ሰራተኞች መረጃ የማረጋገጥ ስራ ላይ ለሚሳተፎ ከማዕከል ከክ/ከተማ እና ከትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አማካሪ አቶ አቡበከር ሀሺም እንደተናገሩት እንደሚታወቀው እንደ ሀገር እንደ ከተማ ተቋማዊ ሪፎርም ተጀምሯል ከሪፎርሙ ፒላሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የዲጂታላይዝ የመንግስት አገልግሎት ተጠቃሽ ነው በውስጡም የተደራጀ የመንግስት ስራተኞች አሁናዊ መረጃን ዲጂታላይዝ ማድረግ ይገኝበታል ብለዋል።
በዚህ መድረክ ላይ የተገኛችሁ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮች ፣ የሰው ሀይል ከፍተኛ ባለሙያዎች የመረጃውን አስፈላጊነት በመረዳት ስለመረጃው ለሰራተኞች ግንዛቤ በመፍጠር ለመረጃ ሰብሳቢዎች የስራ ቦታን በማዘጋጀት፣ ለስራው የሚያስፈልገውን መረጃ በማዘጋጀት ስራውን እንድታስተባበሩ ሲሉ አቶ አብበከር መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ሐዋዝ በበኩላቸው ይህ መድረክ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች መረጃ ማረጋገጥ ስራ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን በማድረግ ቴክኒካዊ አቀራረብን ለማቀናጀት ነው ያሉ ሲሆን በዚህ ስራ ትክክለኛ የሰው ሀይል መረጃን በማረጋገጥ በተቋማት ውስጥ ያሉትን ክፍተት የሚለይ አስተማማኝ ዲጂታል የሰው ኃይል መረጃ ቋት ለመፍጠር፣ ወደ ዘመናዊ እና የተረጋገጠ የሰው ሀይል ስራ አመራር ስርዓት ለመሸጋገርና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመቅረፅ የሚያስችል ጥራት ያለው የሰው ሀይል መረጃ ለማደራጀት መሆኑን ገልፀዋል።
ስለስራው አጠቃላይ ይዘት፣ ስነ-ዘዴ፣ በስራ ላይ የሚውሉ ዲጂታል የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችና በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ላይ ገለጻ ቀርቦ ግንዛቤ ተፈጥሮበታል።
በግንዝቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ከክ/ከተማ እና ከትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።