ፐብሊክ ሰርቪሱ ከየት ወዴት
እንግዲህ ከተማችን ከተቆረቆረች ወደ አንድ መቶ አርባኛ ዓመት ሊሞላት እጅግም ነው የቀራት፡፡ እንደእድሜ ጠገብነቷ የአገርኛ ከተሞችን እየመራች ተሞክሮዋን እያካፈለች እና ያላትን ልምድ እየለገሰች እዚህ ደርሳለች፡፡ አዲስ አበባችን በተለያየ ጊዜያት የተለያዩ የአስተዳደር ዘይቤ ስትመራ በመቆየቷ አሁን ካለው ሁሉን አካታች ፌደራላዊ መንግሥት አወቃቀር ጋር የተጣጣመ የመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር እንዲዋቀር እስከተደረገበት ጥር ወር 1985 ዓመተ ምህረት ድረስ የከተማዋን የሠው ኃይል የሚያስተዳድር አደረጃጀትና ተቋም አልነበራትም፡፡
በ1927 ዓ/ም በወጣው አዋጅ ለከተማዋ አስተዳደር ተግባርና ኃላፊነት በህግ ቢደነገግም ከጣሊያን ወረራ በኋላም በአዋጁ ቁጥር 1/1942 መሠረት በንጉሱ የሚሾም ከንቲባና 8 አባላት ያሉት ካውንስል ተቋቁሞ ተጠሪነቱ ለንጉሱና ለአገር ግዛት ሚኒስቴር ሆኖ የተደራጀ ነበር፡፡
በተለይም በማዘጋጃ ቤቱ ሥር ስላሉት የመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ትኩረት የሰጠ ካለመሆኑም በላይ በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የሚያገለግሉ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር በከተማዋ ከንቲባና ሌሎች የሥራ ኋላፊዎች በጎ ፈቃድ የሚከናወን እንደነበር በሠራተኞቹ ማህደር የተያያዙት አቤቱታዎችና የተሰጣቸው ውሳኔዎች ያስረዳሉ፡፡
በትዕዛዝ ቁጥር 23/1954 መሠረት በተቋቋመውና በሰኔ ወር በ1955 ሥራውን በጀመረው የመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት በሚወጡ የሠው ኃይል አስተዳደር ደንብና መመሪያዎች መሠረት የሠው ኃይል አስተዳደር ተግባራትን ያከናወኑ ነበር፡፡
በተማከለ አስተዳደር ሥር የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ሰርቪስን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስተዳድር ቢሮ የተቋቋመው፣ ከወታደራዊው ደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ አገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው የሽግግር መንግሥት በመላ ሃገሪቱ ውስጥ በተወሰዱ መሠረታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ማግስት ነው፡፡
በከተማችን የመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ቢሮ በጥር ወር 1985 ዓ/ም ተቋቁሞ ሥራውን የጀመረው አንድ የቢሮ ኃላፊ ተሾመውለትና ከፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ኮሚሽን ከ15 የማይበልጡ ሠራተኞች በዝውውር በተመደቡለት ሠራተኞች ነበርና ዋና ተግባራቸውንም ማከናወን ጀመሩ፡፡ በዚህም ሁለቱ መምሪያዎች የሥራ ምደባና አበል ጥናት መመሪያ እና የሠራተኛ ሥምሪት መምሪያ መተግበር ሲሆን በሁለተኛነት የተጠቀሰው መምሪያ በሁለት ቡድኖች እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡
በሁለቱ መምሪያዎች ሥር የቅጥርና ዝውውር ቡድን እና የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ ጭማሪ ቡድን አማካኝነት ወደ ሥራው በመግባት ባለው የሠው ኃይል መጠን እና ያሉትን ሠራተኞች በመደልደልና በማሰማራት በርካታ የሠው ኃይል አሰተዳደር ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ቢሮው ምስረታውን ተከትሎ የሠው ኃይል ከማደራጀት፣ አቅም ከመገንባት እና ከማሰማራት ባሻገር ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ የመስተዳድሩ የመንግሥት ሠራተኞች /ከ2ዐ ሺህ በላይ የሚሆኑ/ የሥራ ምደባና የመዋቅር ጥናት፣ በመስተዳድሩ ዓላማ አስፈፃሚ ቢሮዎች የተደለደሉ ሠራተኞችን ተፈላጊ ችሎታ መሟላት በማጣራት መመዝገብ፣ የባለሙያ ሠራተኞች ቅጥርና ምልመላ ተግባራት የገኙበታል፡፡
ቢሮው የተሟላ መዋቅርና የሠው ኃይል በማካተት የተዋቀረ ባለመሆኑ ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 41/85 የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት መወጣት በሚያስችል ደረጃ ላይ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ቢሮው በወቅቱ በተለይም የዲሲፒሊን ይግባኝ ለማየት የሚያስችል ችሎት እና የሠራተኞችን ቅሬታና አቤቱታ የሚያጣራ የሥራ ክፍል ባለመሟላቱ ይቸገር እንደነበር በወቅቱ የነበሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ትውስታ አብነት ይሆነናል፡፡ በዚህ ረገድም የሚቀርቡ ጉዳዮችን በሚመለከት በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ኮሚሽን የሥራ ዕገዛ ይደረግለት እንደነበረ ሳይጠቀስ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡
መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎረም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደበት ጊዘም ከሪፎርሙ አምስት ንዑሳን ኘሮግራሞች መካከል አንደኛው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሚመራው የሠው ኃይል ማሻሻያ ንዑሳን ኘሮግራም በስሩ 7 ኘሮጀክቶችን አዋቅሮ ሥራ ሲጀምር የራሱን መርሃ ግብር ነድፎ ተንቀሳቅሷል፡፡
ይህ በእንዲህ አያለ በ1995 ዓ/ም በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 የአዲስ አበባ ከተማ በቻርተር አንድትተዳደር ሲወሰንና ተገልጋዮን ህብረሰብ ፍላጎት የሚያረካ አገልግሎት አሰጣጥ በየአቅራቢያው እንዲያገኝ የሚያደርግ አሠራር በ1995 ዓ/ም ሲዘረጋ፤ ቢሮውም በእዋጅ ቁጥር 2/95 መሠረት አዲስ ሰያሜና አደረጃጀት ተዘጋጅቶለ ወደ ትግበራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
በከተማዋ የተካሄደው የማስተር ኘላን ከለሳ ጥናት መሠረት ቀደም ሲል በአራት የሥልጣን እርከን ደረጃ ማለትም በ6 ዞን በ28 ወረዳና 299 ቀበሌዎች የነበረውን አደረጃጀት በአሥር ክፍለ ከተማ እና በ99 ቀበሌዎች እንዲደረጁ በመወሰኑ የሠው ኃይል አስተዳደሩም በአሥሩም ክፍለ ከተሞች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ ተደራጅቷል፡፡
ከዚህም ቢሮውም ስያሜው ተቀይሮ ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ በሚል የተዋቀረና ተጠሪነቱም ለአቅም ግንባታ ቢሮ እንዲሆን ተደርጎ ተደራጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣኞች አንዱ የከተማዋን ልዩ ባህሪ ያገናዘበ የሠው ኃይል አስተዳደር ደንብና መመሪያዎችን ማውጣት በመሆኑ የከተማዋን ባህሪ ያገናዘቡ የሠው ኃይል አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 3/95 እና አዋጁን ተከትሎ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል፡፡
የከተማዋን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት አሠራርና የሥራ ሁኔታዎች በማሻሻል የከተማዋን ዕድገትና ልማት ለማፋጠን ከተወሰዱት እርምጃዎች ጋር የተያያዙ የአሠራርና የማስፈፀሚያ ስልቶች ማሻሻያ ተግባራት ተከናውኗል፡፡ የተለያዩ መመሪያዎች ማለትም የቅጥር የዝውውር፣ የዲሲፒሊን አፈፃፀም፣ የሥልጠና መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ ሥራዎች የተከናወኑበት ዋናው ዓላማ ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የአገልጋዩን የማፈፀም አቅም በማጎልበት ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ እና ተገልጋዩ ህብረተሰብ ተገቢውን አገልግሎት ከመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲያገኝ ለማድረግና የሚከናወኑ የሠው ኃይል አስተዳደር ተግባራት የሚያሳድሩትን ቅሬታ ለማስወገድና የሠራተኞችን ተነሳሽነት በመጨመር መንግሥታዊ የልማት ሥራዎች በቁጠባና በቅልጥፍና ለማከናወን ቢሆንም ዘላቂነት ያለው ውጤት አስገኝቷል ማለት አያስደፍርም፡፡
ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ የተካሄዱት የለውጥ እንቅስቃሴዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እየሄደ ባለበት ወቅት በ1997 የተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ውጤት ተከትሎ እስከ 2000 ድረስ የተጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት የቀድሞ አስተሳሰብና ድርጊት በመመለሱ ምክንያት ሲቪል ሰርቫንቱ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የአገልጋይነት ስሜት ተቀዛቅዞ ታይቷል፡፡
በዚህም በከተማዋ የነበሩ ዘርፍ ብዙና ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የከተማዋን የፐብሊክ ሰርቪስ ሪፎርም እንቅስቃሴ በማጠናከር ለውጡን በአስተማማኝ መሠረት ለመጣል የተሠራው ሥራ ያዝ ለቀቅ እየተደረገ አመታትን ማስቆጠር ቢጀምርም፤ እንደከተማ የተቀናጀ የማስፈፀም አቅም ግንባታ ኘሮግራም ተቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡
በዚህም የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተሻለ አቅም ለማከናወን ከከተማችንና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ የለውጥ መሳሪያዎች በመምረጥና ተግባራዊ በማድረግ የመንግሥት ተቋማት ቀልጣፋ ውጤታማና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራ ተሰርቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪሱ ለነዋሪው ግልፅ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለመስጠትና የተገልጋዩን ህዝብ እርካታ ለማረጋገጥ የተካሄደው የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
በከተማዋ በተካሄደው የመሠረታዊ የአሠራር ሂደት ለውጥ ጥናት በወቅቱ 67/ ስልሳ ሰባት/ ዋና እና 6/ ስድስት/ ደጋፊ የሥራ ሂደቶች ግልፅ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የአስራር ሂደቶችም ከተገልጋይ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ከውጣ ውረድና እንግልት ለማላቀቅ ቁልፍ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በወረዳ ደረጃ እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡
ለዚህም ተግባር የሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ የተሟላ የሠው ኃይልና አደረጃጀት እንዲኖራቸው ተገቢውን እገዛ በማድረግ በከተማዋ ለሚካሂደው የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ እየተወጣም ይገኛል፡፡
በተለይም በሠው ኃይል አቅርቦትና ብቃት በማሳደግ ረገድ ኤጀንሲው የከተማ አስተዳደሩን የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ መሆኑ ሳይነሳ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ኤጀንሲው በተዋቀሩ አደረጃጀቶች ላይ ተገቢውን አመራርና ፈፃሚ የመመደብና ከ12 ሺህ በላይ አዳዲስ ምሩቃን ወጣቶችን በመቅጠር የሰው ኃይል አቅርቦትን ከማሳደጉም በተጨማሪ የአመለካከትና የአፈፃፀም ብቃት የሚያጎለብቱ የሠው ኃይል ልማት ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በሶስት የሥልጣን እርከኖች የማስተዳደሩን ተግባርና አገልግሎትን የማሻሻል አካሄድ ሲወሰንና ቀበሌዎች በወረዳ የመተካቱ ተግባር ሲከናወን፣ ኤጀንሲው አካሄድ ሲወሰንና ቀበሌዎች በወረዳ የመተካቱ ተግባር ሲከናወን ኤጀንሲው የ116 ወረዳዎችን/ ኋላ ላይ እስከ አንድ መቶ ሃያ አንድ ምክር ቤት አልባ ወረዳዎች ተጨምረው ነበር/ አደረጃጀትና የሠው ኃይል በማጥናት ከ2ዐ የማይበልጥ ሠራተኛ የነበረውን የቀበሌ አደረጃጀት በመቀየር ከ100-150 የሠው ኃይል በማሟላት ወረዳዎች በአደረጃጀትና በአሠራር ተጠናከረው ለአገልግሎት አሰጣጣቸው ብቁ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት በአቅራቢያው የሚገኝበትና የሲቪል ሰርቪሱን አሰራርና አደረጃጀት ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ከላይ እስከታች መልክ የማስያዝ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ይህም ለብልሹ አሠራር እና ለሌብነት ተግባር ምቹ እንዳይሆኑ በማድረግና ህብረተሰቡ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ፍትሃዊ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የበኩሉን እገዛ አድርጓል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በ2010 በአገር ደረጃ የተካሄደውን ሃገራዊ ለውጥ መነሻነት በርካታ የሪፎርም ተግባራት መከናወናቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል በፐብሊክ ሰርቪሱ አይነኬ እና አይደፈሩ ተብለው በይደር ያደሩ ጉዳዮች እና ተከድነው ይብሰሉ እና ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለው የከረሙ የሠራተኛው የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች (የሠራተኞች የቤት ኪራይ፣ የካፍቴሪያ ተጠቃሚነት፣ የህፃናት ማቆያ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት) በጅምር ደረጃም ቢሆን የታዩበትና ምላሽ የተሰጠበት ወቅት እንደነበር አለማውሳት አይቻልም፡፡
ከተማ አስተዳደሩ አዳጊውን የህብረተሰብ የአገልግሎት ፍላጎት መነሻ ያደረገ አሠራር እና አደረጃጀትን በመዘርጋት አላሰራ ያሉ ደንቦችና መመሪያዎችን በማሻሻል፣ የከተማ አዋጅ 56/2010 መነሻ በማድረግ በ2011 የሠራተኞች የድልድል አፈፃፀም መመሪያ ሚያዚያ 2011 ዓ/ም፣ የነጥብ የሥራ ምዘና የሠራተኞች ድልድል አፈፃፀም መመሪያ (JEG) ሐምሌ 2011፣ 79/2014 እና 136/2015 የሠራተኞች የድልድል መመሪያ በማሻሻል መውጣቱ እና የአዲስ አበባ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 ተበታትነው የነበሩ አገልግሎቶችን የሥራ ፍሰት ባህሪያቸውን መነሻ በማድረግ አስፈፃሚ አካላትን በማሰባሰብ ወደ 46 ተቋማት ዝቅ እንዲሉ በማድረግ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ከተማ አስተዳደሩ በተመረጡ 16 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለማስተግበር የወጣውን ደንብ ቁጥር 156/2016 መነሻ በማድረግ የብቃት እና የባሕሪ ፈተና እንዲወስዱ በማድረግ እና የፐብሊክ ሰርቪሱን አካታችነት ባሟላ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሠው ኃብት ልማት ቢሮ በተለያዩ አደረጃጀቶች እና ስያሜዎች ይጠራ እንደነበር የተቋሙ አንዱ ታሪካዊ ዳራው ሲሆን ቀደም ሲል ሲቪል ሰርቪስ፣ አቅም ግንባታ ቢሮ እና የአሁን ስያሜውን የፐብሊክ ሰርቪስና የሠው ኃብት ልማት ቢሮ በሚል ስያሜ ሲጠራ እንደነበር እና ዋና ዋና ተግባራቱም ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የአቅም ግንባታ ቢሮ የቀረበውን ጥናት ከተቀበለ በኋላ ለካቢኔ አቅርቦ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት እኛም ልናከናውናቸው የሚገቡ በርካታ የሠው ኃይል ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ ተግባራት ስኬት የከተማዋን የመልካም አስተዳደር፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ለማሳካት ጉልህ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
ስለሆነም በፐብሊክ ሰርቪሱ ውስጥ የተገኙትን የአገልግሎት መሻሻል ሁኔታዎች ቀጣይነት ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በ16 ሴክተሮች ላይ የተጀመረው የሪፎርም ሥራዎች በተግባር አፈፃፀም የታዩ ክፍተቶችን በማረም፣ ጠንካራ ጎኖችን ቀምሮ ወደ ሁሉም ተቋማት በማፋት ብቃት ያለው የሠው ኃብት በከተማ አስተዳደሩ ተሟልቶ እንዲገኝ የማድረጉ ሥራ በስፋት ሊኬድበት ይገባል፡፡
ፐብሊክ ሰርቪሱ አገልግሎት አሠጣጡን ውጤታማ ለማድረግ የሠው ሀብት መረጃ አያያዝ እና ተያያዥ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ (ኢስሚስ) እንዲደገፍ ማድረግ ወቅቱ የተደረሰበትና የመረጃ ልውውጦች ከወረቀት አሠራር እንዲላቀቁ የሚያደረግና የፈጣን አገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህም አንጻር የተቀናጀ የፐብሊክ ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከማዕከል እስከ ወረዳ እና በ338 ትምህርት ቤቶች፣ በ6 ሆስፒታል እና በ111 ጤና ጣቢያዎች በሚገኙ 622 ተቋማት ውስጥ የ161,463 / አንድ መቶ ስድሳ አንድ ሺ አራት መቶ ስድሳ ሶስት/ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃን ወደ ሲስተም የማስገባት ሥራ እና ይህንን አዲስ የሠው ኃብት የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለመተግበር በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ የተቀረጸውን ሞጁል እና የለማውን ቴክኖሎጂ በስፋት በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪሱን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ከማዘመን ጎን ለጎን የአስተዳደር ፍርድ ቤት አገልግሎትን ለማሻሻል እና የተፋጠነ የፍትህ የሰፈነበት ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባት አገልግሎቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ እንዲቻል ከ2012 ወዲህ የዳኞችን ቁጥር በማሳደግ እና ችሎቱን ከአንድ ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ፣ ተገልጋዮች የክስ ማመልከቻቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው በቴሌግራም ቦት መረጃ መለዋወጥ እንዲቻል ማድረግ ተችሏል፡፡
ቢሮው የሠው ኃብት አመራር ልህቀት፣ የማስፈፀም አቅም ግንባታ ልህቀት እና የአገልግሎት አሠጣጥና ስታንዳርዳይዜሽን ልህቀት ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች በማድረግ በከተማዋ ያለውን ፐብሊክ ሰርቪስ የዘመነ ለማድረግና ዲጂታል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመፍጠር ከሚያከናውናቸው ዓበይት ተግባራት ጎን ለጎን እንደቢሮ የተሰጡትን ግቦችን ለማሳካት በተያዙት የማስፈጸሚያ ስልቶች (Initiatives) የወረዳ የማስፈፀም አቅም ግንባታ (Smart Woreda development) ፕሮጀክት እና የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት ፕሮጀክት /competency based framework/፣ የተቀናጀ የሰው ሀብት መረጃ አያያዝ ስርዓት /ICSMIS/ ትግበራ ፕሮጀክት በዋናነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የአዲስን ትውልድ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት ከተያዘው ሁለገብ አቅጣጫ አኳያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ ባሳለፈው ውሳኔ በመንግሥት የአገልግሎት እና አስተዳደር ፖሊሲ መንግሥት የሚያወጣቸውን ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመፈፀምና ለማስፈፀም ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡
በዚህም ፖሊሲው ሊፈታቸው የተገባ ሰባት ምሰሶዎች ውስጥ ከሆኑት ማለትም፡- ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ መገንባት፣ ብዙኃንና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ማፋጠን፣ የመንግሥት አደረጃጀትና አስተዳደር ሥርዓትን ማሳለጥ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግሥት አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት፣ የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት መገንባትና የማስፈፀም አቅምን ማሳደግ፣ ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ቅቡልነት ያላቸው አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ፣ የሲቪል ሰርቪስ ገቢር ነቢብ አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን ላይ ያተኮረ በመሆኑ ፐብሊክ ሰርቪሱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈ ተቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለማየት ዙሪያ መለስ ተግባራን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ባሁኑ ወቅት 168ሺህ066 የሚሆኑ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች የከተማዋን የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እያከናወኑ የሚገኙ ቢሆንም የከተማዋ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ውጤታማ ለማድረግ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት እና የኑሮ ደረጃ አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግሥታዊ አገልግሎት ዕርካታ ከፍ እንዲል ማድረግ እና በሂደት ፐብሊክ ሰርቪሱ በአገልግሎት አሠጣጡ እና በሁለንተናዊ ውቅሩ ተዓማኒነት ያለው ተቋም ተገንብቶ ለማየት የሁላችንን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገንዝበን ለውጤታማነቱ ከዚህ በላይ በትጋት መሥራት ይገባናል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሠው ኃብት ልማት ቢሮን በዓመታት መሃል የመሩ አመራሮች ለትውስታ
-
ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲን ለረጅም ጊዜ አቶ ዘገየ የማነብርሃን የመሩት ከጥር 8/2000 እስከ 2009፣
-
አቶ ዳባ ደበሌ ከ 2000 እስከ 2002
-
አቶ አባተ ስጦታው ከ 2002 እስከ 2003
-
አቶ ይስሃቅ ግርማይ ከ 2003 እስከ 2010
-
ዶ/ር ፍሬሕይወት ገብረሕይወት ከ 2010 እስከ 2012
-
አቶ ኃይሉ ሉሌ ከ 2012 እስከ 2014
-
ወ/ሮ ሂክማ ኸይረዲን ከ 2014 እስከ 2016፣
-
ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ከጥር 2016 እስከ ግንቦት 2016፣
-
ዶ/ር ጀማሉ ጀምበሩ ከግንቦት 2016 እስከ ……
ምንጭ፡- ከቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቭል ሰርቪስ ኤጀንሲ ሠነዶችና ሌሎች አመታዊ ስታትስቲክስ መረጃ፣