በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 ዓ.ም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት በወጣ አዋጅ ቁጥር 84/2016 መሰረት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ እንደገና የተቋቋመ ሲሆን ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መነሻ ለተገልጋዮቹ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በአዲስ መልክ በመለየት አደራጅቷል፡፡ ቢሮው በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩን የመንግስት ሰራተኞች የማብቃት፣ የማስተዳደር፣ የከተማውን የመንግስት ተቋማት አደረጃጀት ማጥናትና የመከለስ እና የስራ አመራር ስርዓት ትግበራውን የመደገፍና የማማከር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ይህንን ኃላፊነትም በብቃት ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማዘጋጀትና በማሟላት በተገልጋዮች ጥያቄና ፍላጎት መሰረት የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ቢሮው የሚሰጠው አገልግሎት የተገልጋይ ፍላጎትን ማዕከል አድርጎ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል የሚሰጡ አገልግሎት አይነቶች፣ አገልግሎቱ የሚሰጥበት ስታንዳርድ፣ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ቦታ እና ከተገልጋይ የሚጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎችን በግልጽ በዝርዝር በማስቀመጥ የቢሮው አመራሮችና ሠራተኞች ሊተገብሩትና ሊከተሉት የሚገባ ይህ የዜጎች ስምምነት ቻርተር ተዘጋጅቷል፡፡
የቢሮው ስልጣንና ተግባር
1.የተቋም አቅም ግንባታ ስራን የሚያሳልጡ ዘመናዊ አሰራሮችንና ተሞክሮዎችን በመለየት በከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ አስፈላጊዉን የቴክኒክና የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፤
2. በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች የሰዉ ሀብት ልማት በቀጣይነት የሚለማበትንና ጥቅም ላይ የሚዉልበትን ስርዓት ይዘረጋል፤ይተገብራል፤እንዲተገበር ያደርጋል፤
3. የተቋማት አደረጃጀት ጥናት ላይ አስፈላጊዉን ድጋፍ ይሰጣል፤ ያማክራል፤ አግባብነቱን ይመረምራል፣ ያጸድቃል፤
4. የከተማው አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባራት ጥናት ያካሂዳል፤ ውጤቱን ለካቢኔ ያቀርባል፣ ሲጸድቅም ተገቢዉን ይፈጽማል፤
5. በከተማው አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ተገቢዉ ስታንዳርድ መኖሩን ያረጋግጣል፤ እንዲያዘጋጁ ያደርጋል፤ ያጸድቃል፤ ተግባራዊ መደረጉን ያረጋግጣል፤
6. በከተማው አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ አፈጻፀም ይከታተላል፣ የተገልጋዩን እርካታ ጥናት ያካሂዳል፣ የጥናቱን ውጤት ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፤
7. የመንግስት ሰራተኞች ቅሬታ አቀራረብና አፈታት ስርዓት ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለዉ መንገድ መዘርጋቱንና ተግባራዊ መደረጉን እንዲሁም ዉጤታማነቱን ያረጋግጣል፤
8. ያልተማከለ የአስተዳደር ስርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል የማስፈጸም አቅም ግንባታ ይዘረጋል፣ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፣ ይደግፋል፤
9. የመንግስት ሰራተኞችን ወቅታዊ አፈፃፀም ምዘና የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል፤ ተግባራዊነቱንም ያረጋግጣል፤
10. የመንግስት ሰራተኛ በብቃትና በአፈጻፀም ላይ የተመሰረተ የምደባ፣ የደረጃ ዕድገትና የእርከን ጭማሪ፣ የጥቅማጥቅምና የማበረታቻ ስርዓት ይዘረጋል፣ እንዲተገበር ያደርጋል፤ ውጤታማነቱን ይገመግማል፣ አስፈላጊዉን የማሻሻያ እርምጃ ይወስዳል፤
11. አግባብ ያለው የፌደራል ሕግ እንደተጠበቀ ሆኖ ለመንግስት ሰራተኛዉ የሚያስፈልጉ የስራ መደቦች፣ የትምህርት የስልጠናና የስራ ልምድ አጠቃላይ መመዘኛዎች ያወጣል፤
12. የመንግስት ሰራተኞች አቀጣጠር፣ አመዳደብ፣ የደረጃ እድገት፣ ዝውውር፣ አበልና ጥቅማ ጥቅም፣ ስልጠናና የዲሲፕሊን አፈጻጸም መመሪያ ያወጣል፤ በህግ መሰረት መፈጸሙን ያረጋግጣል፤
13. በህግ መሰረት የከተማ አስተዳደሩን የመንግስት ሰራተኞችን ከጡረታ ዕድሜ ክልል በላይ በአገልግሎት ላይ ለማቆየት በሚቀርብ ጥያቄ ላይ ዉሳኔ ይሰጣል፤
14. የከተማ አስተዳደሩን የሰዉ ሀብት መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ያደራጃል፤
15. የህዝብ አገልጋይነት አስተሳሰብ ያለዉ አመራርና ፈጻሚ ይገነባል እንዲገነባ ይሰራል፣ የብቃት ማረጋገጫ ስርዓት ይዘረጋል፣ ተግባራዊነቱንም ይከታተላል፣ ይደግፋል፤ ያረጋግጣል፤
16. በሚዘረጋቸው አዳዲስ አሰራሮች፤ አደረጃጀቶችና ማኑዋሎች ዙሪያ አጫጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ እንዲሰጥ ያደርጋል፤
17. ሁሉም ተቋማት ዉጤታማ አፈጻፀም እንዲኖራቸዉ የሚያደርጋቸዉን አዳዲስ የለውጥ መሳሪያዎች ከራሳቸዉ ባህርይ አንጻር አጥንተው እንዲያቀርቡ ያበረታታል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊ መሆኑን ይከታተላል፣
18. የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ አፈጻጸም ውጤታማነት ይመራል፣ አፈጻጸማቸውን ይገመግማል፣ ግብረ- መልስ ይሰጣል፣ ደረጃ ያወጣል፣ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ይልካል፣
19. ከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ላይ የሰራተኞች አፈጻጸም ምዘና ተግባራዊ እንዲሆን ሥርዓት ይዘረጋል፣ አፈጻጸሙን በመፈተሸ ግብረ-መልስ ይሰጣል፣ የምዘና ሂደቱ በበላይነት ያስተባብራል፣ ያረጋግጣል፡፡